በ12ኛ ዙር የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የምረቃ ስነ-ስርዓት በዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኪሮስ ጉዕሽ የቀረበ መልእክት

ክቡር ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ እና የዕለቱ የክብር እንግዳ

የተከበራችሁ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የአመራር አባላት

የተከበራችሁ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ

ውድ ዕጩ ተመራቂዎች

የተከበራችሁ ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች

ክቡራትና ክቡራን ዩኒቨርሲቲ

ከሁሉ አስቀድሜ ኮሮና ቫይረስ ያስከተለውን ከባድ ተፅዕኖ ተቋቁማችሁ ለምርቃ ቀናችሁ ለደረሳችሁ ተመራቂዎች፣

ተመራቂዎቻችን በዚህ ሁኔታ ሆነው ለምርቃ ላደረሷችሁ መምህራን እና የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦች በራሴ እና በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ስም እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ ።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአገራችን መግባቱ ከተረጋገጠ በኋላ የወረርሽኙን ስርጭት ለመቀነስ የመማር መስተማሩ እንዲቋረጥ እና ተማሪዎች ወደየቤተሰቦቻቸው እንዲሸኙ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በወሰነው መሰረት አክሱም ዩኒቨርሲቲ በሁሉም ፕሮግራሞች ለሁለተኛ ወሰነ ትምህርት ተመዝግበው ትምህርታቸውን በመከታተል የነበሩ ተማሪዎች የገፅ ለገፅ ትምህርት በማቆም መደበኛ ተማሪዎች በጉዘው ሂደት ላይ ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ በማሰብ በዩኒቨርሲቲ ወጪ በርካታ አውቶብሶችን በመከራየት ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደየ መጡበት የዞን ከተማ ማድረስ ችለናል።

ተማሪዎቻችን የመሸኘት ስራ እንደተጠናቀቀ የቫይረሱ ስርጭት እና በማህበረሰባችን የሚያስከትለው ተፅእኖ መቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች ለመስራት የሚያስችል አደረጃጀት በመፍጠር ወደ ስራ ተገብቷል።

በዚህ መሰረት ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ፣ ከትግራይ የጤና ምርምር ተቋም፣ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ተቋም፣ ከአከባቢ የዞን እና ከተማ መስተዳድሮች እና በአከባቢው ከሚገኙ የጤና ተቋማት ጋር በመተባበር:

  1. ለበርካታዜጎችየለይቶማቆያአገልግሎትየሚሰጡማእከላትበአክሱም፣ሸረእናዓድዋግቢዎቻችንአደራጅተናል።
  2. በአክሱምእናሸረግቢዎቻችንየተቋቋሙትየህክምናየማገገሚያማእከላትለበርካታቫይረሱየተገኘባችውዜጎችአገልግሎትእየሰጡይገኛሉ።
  3. በአክሱም ጤና ሳይንስ እና ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የCOVID-19 የመመርመርያ ማእከል በመክፍት የምርመራ አገልግሎት እየሰጠን እንገኛለን።

ከዚህ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው በመደበው በጀት እና የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ከደመወዘችው ባዋጡት ገንዘብ ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎት እና ድጋፍ ስራዎች ስንሰራ ቆይተናል። በቀጣይም አጠናክረን እንቀጥላለን።

በዚህ አጋጣሚ ወረርሽኙ ለመከላከል በምናደርገው ጥረት ፊት ቁመው እየታጋሉ ላሉ የጤና ባለሙያዎቻችን እና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞቻችን ያለኝን አድናቆት እና ክብር እየገለፅኩ ትግላቸው አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት እተማመናለሁ። በዚህ ትግል ውስጥ ለትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ በሙያቸው ድጋፍ እያደረጉ በነበሩበት ግዜ በቫይረሱ ተይዘው መስዋእትነት ለከፈሉ የስራ ባልደርባችን ዶር ፍስሃ አለምሰገድ የተሰማኝን ጥልቅ ሃዘን በራሴ እና በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ስም ለመግለፅ እወዳለሁ።

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሰራነው ስራ እንደተጠበቀ ሁኖ ቫይረሱ እየተከላከልን የዩኒቨርሲቲውን ተልእኮ ለመሳካት ለተወሰኑ ግዝያት ተቋርጦ የነበረው የድህረ ምርቃ ትምህርት በኦንላይን እንዲቀጥል በተደረገው ጥረት የድህረ ምረቃ ተማሪዎቻችን እና የመምህራኖቻቸው ትጋትና ጥረት ታክሎበት የትምህርት ዘመኑ የሁለተኛ ወሰነ ትምህርት በዚህ ክረምት የተጠናቀቀ ሲሆን የመመረቂያ ፅሑፎቻቸው ስያዘጋጁ የነበሩ የድህረ ምረቃ ተማሪዎቻችን የመመረቅያ ፅሑፎቻቸው ሙሉ በሙሉ በኦንላይን በማካሄድ ለዚህ ምርቃ በቅቷል።

እንኳን ደስ አላችሁ!

በተመሳሳይ መልኩ የህክምና ዶክትሬት ዲግሪ እና ሌሎች የጤና ሳይንስ ተመራቂዎቻችን በሙያቸው ምክንያት ቫይረሱ ለመከላካል ካላቸው ልዩ ተልእኮ በተጨማሪ የቀራቸው ትምህርት በሚገባ አጠናቀው ለዛሬው የምርቃት ቀን በቅቷል።

በአጠቃላይ በ2012 የትምህርት ዘመን በተለያየ ግዜ ትምህርታቸው በሚገባ ጨርሰው ሰኔቱ ያፀደቀላቸው 36 የህክምና ዶክትሬት ዲግሪ እና 674 የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎችን ጨምሮ በድምሩ 3179 ተማራቂዎችን ለምርቃ የተዘጋጁ ሲሆን ከተመራቂ ተማሪዎች 49.3% ሴቶች ናቸው።

ውድ ተመራቁዎች እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩኝ በትምህርት ወቅት ያገኛችሁትን እውቀት እና ክህሎት በስራ ዓለም ላይ በተገቢው መተግበር አገራችን ከድህነት ለመውጣት ለምታደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል የበኩላችሁን አወንታዊ ሚና እንድትወጡ አደራ እላለሁ።

ክቡራትና ክቡራን

አክሱም ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ትውልድ ተብለው ከሚታወቁ ዩንቨርስቲዎች አንዱ ሲሆን የዛሬ ተመራቂዎችን ጨምሮ እስከአሁን 29, 262 ምሩቃን በማስመረቅ በአገሪቱ የዕድገት ጉዞ የብኩሉን ድርሻ ተወጧል በመወጣትም ይገኛል። ዩኒቨርስቲው የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት በርካታ የማስፋፍያ
ስራዎች እየሰራን የሚገኝ ሲሆን በዚህ ዓመት ስራው የጀመረው የአድዋ ግቢ ጨምሮ በአራቱም ግቢዎቹ በመደበኛ፣ በክረምት እና በቅዳሜ-እሁድ መርሃ ግብሮች በወረርሽኙ መከሰት ምክንያ የገጽ ለገፅ ትምህርት አስከቆመበት ድረስ ከ24,000 በላይ ተማሪዎች እያስተማረ ነበር።

በቀጣይ ሌሎች ተጨማሪ አመራጮች በመጠቀም የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነት ለማስፋት ጠንክሮ ይሰራል። የምንሰጣቸው የትምህርት ፕሮግራሞች አግባብነት በየግዜው የሚፈተሽ ሲሆን አሁን ባሉን 71 የቅድመ ምርቃ እና 35
የድህረ ምርቃ ፕሮግራሞች በ 2013 ስራ የሚጀምሩ 3 የPhD ፕሮግራም ጨምሮ 12 አዳዲስ ተጨማሪ ፕሮግራሞች የሚጀምሩ ይሆናል።

ጥራት ያለው የተግባር ትምህርት ለመስጠት ከዚህ ቀደም በርካታ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን የእስካሁኑ ጉዞዋችን በሚገባ ገምግመን በቀጣይ የሰለኽለኻ የምርምር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማእከል ጨምሮ በሁሉም ግቢዎቻችን የመሰረተ ልማት የሟሟላት እና ውስጣዊ ይዘት እና አሰራር የማዘመን ጉዳዮች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚሰሩ ይሆናል።

ክቡራትና ክቡራን

ጥራት ያለው ትምህርት መስጠት እንደተጠበቀ ሁኖ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የማህበረሰቡ ችግሮች በምርምር ለመፍታት በርካታ ስራዎች እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን ከተሰሩ ምርምሮች በዓለም ዓቀፍ ታዋቂ በሆኑ ጆርናሎች የማሳተም፣ የተማራማሪዎቻችን ተሳትፎ እና በትብብር የመስራት ባህል እየዳበረ የመጣበት ፍጥነት ተስፋ ሰጪ ጅምር ተብሎ ሊወሰድ ይችላል።

የሚሰሩ ምርምሮች ዓለም አቀፍ ደረጃቸው የጠበቁ እና የማህበረሰባችንን ችግር በተጨባጭ መፍታት የሚችሉ እንዲሆኑ በቀጣይ የሚሰራ ሲሆን፣ የምርምር መሰረተ ልማት ማሟላት እና ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት፣ የተመራማሪዎች ዓቅም እና ተነሳሽነት የሚጨምሩ ተግባራት በልዩ ትኩረት የሚሰሩ ይሆናል።

በማህበረሰብ አገልግሎት መስክም በዚህ ዓመት በጤና፣ በትምህርት፣ በሕግ ፣ በምህንድስናና ሌሎች ዘርፎች በስፋት የተንቀሳቀስን ሲሆን በሚቀጥሉት ግዚያትም አሰራራችንም የበለጠ በማዘምን እና የማህበረሰባችን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ስራዎች አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል።

በመሰረተ ልማት በኩልም የመማር ማስተማሩ፣ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎቻችን የሚያቀላጥፉ በሁሉም ግቢዎቻችን የላይብረሪ፣ የተማሪዎች መመገብያ፣ ማስተማርያ እና መኖርያ ህንፃዎች፣ የቤተ-ሙከራ እና ዎርክሾብ ህንዎች፣ የመምህራን ቢሮ እና መኖርያ ህንፆዎች፣ የተማሪዎች የስፖርት ማዘውተርያ ስታድዮም፣ የቆሻሻ ማከምያ (Treatment Plant)፣ የአስተዳደር ህንፃ፣ የመንገድ
ግንባታ እና የICT መሰረት ልማት ዝርጋታ በመካሄድ ላይ ሲሆን በአገራችን ባሉት ዘርፈ ብዙ ችግሮች እና የኮንስትራክሽን ሴክተሩ ባለው ድክመት ምክንያት ማለቅ በሚገባው ግዜ ባለማለቁ ለስራዎቻችን ተግዳሮት ፈጥረውብናል።

በአጠቃላይ በዋና ዋና ተልእኮዎቻችን በተገባደደው ሁለተኛው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በነበረን አፈፃፀም ተገምግሞ የቀጣይ የዩኒቨርሲቲው የ10 ዓመት ዕቅድ ዝግጅት በሂደት ሲሆን በሚቀጥሉት ዓመታት የትምህርት ጥራት የሚያስጠብቁ፣ የምርምር ዓቅምና ጥራት የሚያሳድጉ እና የማህበረሰባዊ አገልግሎት እና ድጋፍ የሚያሳድጉ ግብአቶች በሟሟላት እና አጠቃላይ ተቋማዊ ዓቅም
ማሳደግ ልዩ ትኩረት እንደሚስጠው አረጋግጣለሁ።

ውድ ተመራቂዎች፣ መምህራን እና የተመራቂ ቤተሰቦች በድጋሜ እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩኝ የኮረና ቫይረስ ስርጭት አሁንም እየጨመረ የሚገኝ በመሆኑ እና እስከአሁን ባለው ሂደት ከመከላከል ውጪ ሌላ መንገድ የሌለ መሆኑ ተገንዝባችሁ በመከላከሉ ረገድ ጠንክራችሁ እንድትሰሩ ጥሪ አቀርባለሁ። በተለይም በጤናው ዘርፍ እየተመረቃችሁ ያላችሁ ተማሪዎቻችን ድርብ ሓላፊነት እንዳለባችሁ አውቃችሁ
ተግተችሁ እንድትሰሩ ጥሪ እያቀረብኩ ዩኒቨርስቲው የጀመራቸው የመከላከል ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።

የቫይረሱ የመከላከል ስራ እንደተጠበቀ ሁኖ ቫይረሱ እየተከላከልን የድህረ ምረቃ ፕሮግሮሞቻችን በኦንላይን የሚቀጥል ሲሆን የቅድመ ምርቃ ተማሪዎቻችን ወደፊት መንግስት በሚወስነው አኳሃን ለማስቀጠል የቅድመ ዝግጅት ስራዎቻችን አጠናክረን እንደምንቀጥል እየገለፀን ተማሪዎቻችን በያሉበት ሁነው በቻሉት መጠን ሁሉ በትምህርታቸው ዝግጅት እያደረጉ የአከባብያቸው ማህበረሰብ ቫይረሱ
ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት እንድያግዙ፣ ስለ ህዝቦች ሰላም እና አብሮ መኖርን እንድያስተምሩ እና ሌሎች የበጎ አድራጎት ስራዎች እንድያጠናክሩ ጥሬን አስተላልፋለሁ።
በመጨረሻም ዩኒቨርሲቲያችን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖረን ላስቻሉ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ የአከባቢው ማህበረሰብ፣ የአከባቢው መስተዳድር እና ፀጥታ አስከባሪ አካላት ከፍ ያለ ምስጋና ለማቅረብ እወደለሁ።

በድጋሜ እንኳን ደስ አላችሁ!

መልካም የስራ ዘመን!

አመሰግናለሁ!

 

ዶ/ር ኪሮስ ጉዕሽ

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት

Written by