አክሱም ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሃግብሮች ያሰለጠናቸው 3179 ተማሪዎች አስመረቀ

አክሱም ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሃግብሮች ያሰለጠናቸው 3179 ተማሪዎች አስመረቀ

ነሐሴ 17 በተካሄደው የምረቃ ስነ ስርዓት መልእክት ያስተላለፉት የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ አክሱም ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ከመከላከል ጎን ለጎን የድህረ-ምረቃ ትምህርት በተለያዩ የበይነ መረብ አማራጮች እንዲቀጥል በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠ አቅጣጫ መሰረት በመተግበር ለምረቃ ማብቃቱ አድንቀዋል።

ዶ/ር ሳሙኤል አክለውም የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በአጭር ግዜ የሚጠፋ አለመሆኑ በመጥቀስ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮች በመጠቀም ለተማሪዎቹ ይበልጥ ተደራሽ ለመሆን መስራት እንደሚጠበቅበት ገልፀዋል።

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኪሮስ ጉዕሽ በበኩላቸው “ኮሮና ቫይረስ ያስከተለውን ከባድ ተፅዕኖ ተቋቁማችሁ ለምርቃ ቀናችሁ ለደረሳችሁ ተመራቂዎች፣ ተመራቂዎቻችን በዚህ ሁኔታ ሆነው ለምርቃ ላደረሳችሁ መምህራና የተመራቂ ተማሪ ቤተሰቦች እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል።

አክሱም ዩኒቨርሲቲ የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነት ለማስፋት እየሰራ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው 3 የሶስተኛ ዲግሪ ጨምሮ 12 አዳዲስ ተጨማሪ ፕሮግራሞች በቀጣዩ የትምህርት ዘመን እንደሚጀምር ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአምስቱ የዩኒቨርሲቲው ግቢዎች የተጀመረው የትምህርትና ምርምር መሰረተ ልማት ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶ/ር ኪሮስ አስታውቀዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ዶ/ር ኑርዓይኒ መሓመድሓጎስ ከህክምና ትምህርት ቤት 3.77 አጠቃላይ ውጤት በማስመዝገብ እንዲሁም ህክምናን ጨምሮ የተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶች በመስጠት የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የአመቱ የሜዳልያ ተሸላሚ ሆናለች።

 

የ3179 ተማሪዎችን መመረቅ ያበሰሩት የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ሬጅስትራርና አልሙናይ ዳይሬክተር ዶ/ር አብርሃም ሃይሉ ከነዚህም መካከል 674 የሁለተኛ ዲግሪ፣ 36 የህክምና ትምህርት እንዲሁም 2469 የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ከመግባቱ በፊት ትምህርታቸው ያጠናቀቁ የአንደኛ ዲግሪ ተማሪዎች መሆናቸውም ጠቅሰዋል።

  

በዕለቱም አክሱም ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙት እውቀት የህብረተሰቡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በሳይንሳዊ መንገድ ለመፍታት እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል።

Written by